ጅግጅጋ(cakaaranews)አርብ፤ግንቦት 17/2010.ውድድሩ እየተጠናቀቀ ባለው የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን አቅም ከመፈተሽ ባለፈ በግል እና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነትም የተሻለ ያደርገዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮና የጅግጅጋ ትምህርት ጽ/ቤት በጋራ ያዘጋጁት በከተማው ውስጥ በሚገኙት የመንግሥት እና የግል ት/ቤቶች በተውጣጡ 40 ት/ቤቶች መካከል ሲደረግ የነበረው የተማሪዎችን አቅም መፈተሽ የሚያስችል የጥያቄና መልስ ውድድር መጠናቀቁ ተገለፀ።
ውድድሩ የ2010 ዓ.ም በጀት አመት የትምህርት ማጠናቀቂያ ወቅት ሲሆን በ40 የመንግሥት እና የግል ት/ቤቶች ለ1 ወር ሲካሄድግ መቆየቱ ተነግሯል። በውድድሩ ማጠናቀቂያ ዕለትም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም አደን መሀድ ፣ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የት/ቤቶች ርዕሰ መምህራን ፣ ወላጆችና ተማሪዎችም ተገኝተዋል። በውድድሩ የመጨረሻ ምዕራፍ የደረሱትም ከጅግጅጋ 1ኛ እና መለስተኛ ት/ቤቶች መካከል ፋራህ ሞጎል እና ዱዳሂዲ ሲሆኑ ከ2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤቶች ደግሞ የጅግጅጋ ማህበረሠብ ት/ቤት እና ኡመር ቢንኸጣብ ት/ቤቶች ናቸው። በዚህም መሠረት ከ1ኛ እና መለስተኛ ት/ቤቶች መካከል 1ኛ የወጣው ፋራህ ሞጎል ት/ቤት ሲሆን ከ2ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ የወጡት ደግሞ ዱዳሂዲና ሁሴን ጊሬ ት/ቤቶች ሲሆኑ ከግል ት/ቤቶች ደግሞ አልቡሽራ ት/ቤት በአንደኛነት አጠናቋል። በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መካከል በተካሄደው የመጨረሻ ውድድር የጅግጅጋ ማህበረሠብ ት/ቤት በአንደኛነት ሲያጠናቀቅ ኡመር ቢን ኸጣብ ት/ቤት ደግሞ 2ኛ ወጥቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ለእያንዳንዱ አሸናፊ ት/ቤት ተማሪዎች የሽልማት መስጠት ሥነ ሥርዓት ተደረጓል። በዚህም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ት/ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም አደን ሲናገሩ “የዚህ ውድድር ዋና አላማ በክልሉ ያሉ ት/ቤቶችን የትምህርት ጥራት ከፍ ለማድረግ የታሰበ ነው በውድድሩም ከ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የሚገኙ ከ8ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች የተወዳደሩበት ሲሆን በተማሪዎች መካከል የተወዳዳሪነት ስሜትን በመፍጠር ወደ ተሻለ ጥራት እና ብቃት እንዲመጡ ያግዛቸዋል” ብሏል። የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዲናስር አሬስ ስለ ውድድሩ አላማ እና ለተማሪዎቹ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ “ዛሬ ያጠናቀቅነው በጅግጅጋ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ት/ቤቶችን አቅም የሚፈትሽ የጥያቄና መልስ ውድድር ነበር ውድድሩ ለ1 ወር ሲደረግ ቆይቶ ዛሬ በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል ዋና አላማውም የ2010 ዓ.ም የትምህርት ዓመት እየተጠናቀቀ እንደመሆኑ መጠን የተማሪዎችን አቅም ምን ይመስላል የሚለውን ለማየትና በመንግሥት እና የግል ት/ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት መልካም እንዲሆነና የእርስ በእርስ ቅርርብ ለመፍጠር ነው” ብለዋል።
ከአሸናፊ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የተሰማቸውን ደስታ ሲናገሩ “ዛሬ የተሰማኝ ስሜት በጣም ከፍተኛ ነው ምክንያቱም ደግሞ ሳስባቸው የነበሩ ህልሞቼ እውን እየሆኑ አይቻለሁ እና በዚህም የክልሉን መንግሥት ከፍተኛ ሥራ ፣ ጥረት እና የተሃድሶ ለውጦቹ የዚህ ዛሬ የደረስንበት የከተማችን የትምህርት ጥራትና የተወዳዳሪነት መነሻ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል ከዚህም ሌላ በት/ቤቶችም ሆነ በሌሎችም ቦታዎች የሴቶቹ ብቃት እና ተሳትፎ በግልጽ እየታየ ነው የኔ ት/ቤት ይህንን አሸንፎ መምራት በመቻሉ በጣም ደስ ብሎኛል” ብሏል።
በመጨረሻም ይህ በጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር የተደረገው የት/ቤቶች ውድድር የተማሪዎችን አቅም ከመመዘን ባለፈ የእርስ በርስ የተወዳዳሪነትን ስሜት በመፍጠር ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት ሲያስችል በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥትና በግል ት/ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ በማቀራረብ ልምድና ክህሎቶችን ለመለዋወጥ መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር ተገልጿል። ዝግጅቱንም የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ት/በሮ እና የጅግጅጋ ከተማ ጽ/ቤት በጋራ አዘጋጅተውታል።