ቀብሪደሀር(Cakaaranews)እሁድ፤ግንቦት 12/2010 ዓ.ም በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ የተገኘውን የሠላም ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ለማጠናከር ሁሉም የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች የተሳተፉበት የሠላምና የልማት ኮንፈረንስ በቀብሪሀደር ከተማ ተካሄደ። በመድረኩም ላይ የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ በድሪ ዩሱፍ ፣ የዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ኪፋህ መዓሊን ፣ የጅግጅጋ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ካሚል አብዲላሂ ሃይቤ እና የቆራሄይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ በተጨማሪም የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዩሱፍ ሀሰን እንዲሁም ሌሎች የክልልና የዞኑ ከፍተኛ አመራር አካላት ተገኝተዋል።
በተጨማሪም መድረኩን የመሩት የኢ.ሶ.ክ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ በድሪ ዩሱፍ ባለፉት ዓመታት በክልሉ በሁሉም የልማት ዘርፎች የተከናወኑትን ስኬቶች ማስቀጠልና በአሁኑ ወቅት ክልሉ ለደረሰበት የልማት ጎዳ የክልሉ ወጣቶች ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ በመግለፅ ክልሉ ያሳከቸዉን የልማት ሥራዎች በአንዳንድ የክልሉን ዕድገት በማይወዱ አካላት እየተከናወኑ ባሉ የልማት ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ የክልሉም ሆነ የቀብሪሀደር ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በንቃት መከላከል እንዳለባቸው ጥሪያቸዉን አቅርበዋል፡፡
አያይዞም በቀብሪደሀር ከተማ አስተዳደር በጥቂት ዓመታት ከተከወኑ የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ቀብርደሀር ዩኒቨርሲቲ ፣ የቀብሪደሀር ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ ፣ የሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮችም ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ም/ቢሮ ኃላፊው አቶ በድሪ ዩሱፍ ።
በሌላ በኩል በክልሉ በተለያዩ የሀላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ የአመራር አካላት የኢ.ሶ.ክ. ባለፉት ዓመታት በሁሉም የልማት ዘርፎች ውጤታማ ስኬቶችን በመጎናፀፍ ክልሉ በአሁኑ ጊዜ በልማት ጎዳና ላይ መሆኑን በመግለፅ ፤ እንዲሁም ክልሉ ያሳከቸዉ የልማት ሥራዎች የማይዋጥላቸው የተለያዩ ፀረ-ልማት አካላት ለክልሉ የልማት ሥራዎች እንቅፋት እንዳይሆኑ መከላከል እንዳለባቸው ለወጣቶቹ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ አያይዘውም ኃላፊዎቹ በክልሉ የተጀመረዉን የሠላም ፣ የልማት ፣ የመልካም አስተዳድርና የህዳሴው የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖራቸው የቀብሪዳሃር ወጣቶች የድርሻቸዉን እንዲወጡና ቀጣይነታቸዉን እንዲያረጋግጡ ጥሪያቸዉን አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የቀብሪዳሃር ከተማ አስተዳድር ወጣቶች በበኩላቸው በክልሉ እየተከናወነ ያለዉን የሠላም ፣ የልማት ፣ የመልካም አስተዳድርና የህዳሴውን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉና ከክልሉ መንግሥት ጎን ቆመው የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡ አያይዞም ወጣቶቹ በክልሉ እየተመዘገቡ ያሉትን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች የማይዋጥላቸው የተለያዩ ፀረ-ልማት ሀይሎችን እንዲሁም በክልሉ የልማት ሥራዎች ላይ እንቅፋት ለመሆን የሚሞክሩ አካላትን እንደሚከላከሉ እና እንደሚዋጉም ተናግረዋል፡፡