ጅግጅጋ(Cakaaranews)ማክሰኞ፤ሰኔ 05/2010ዓ.ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች 8ኛ ቅርንጫፉን መክፈቱ ተገለፀ። በምርቃት ስነ-ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር በክብር እንግድነት በተገኙበት እንዲሁም የመንግሥት ከፍተኛ አመራር አካላት፣ሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው በተገኙበት የቅርንጫፉን መከፈት አብስሯል። የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መመሪያ በጅግጅጋ ከተማ መከፈቱ በክልሉ ለሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ለክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች የትውልድ ካርድ መስጠትና ማደስ ብሎም ለውጭ ሃገር ዜጎች የኦንላይን ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ ለመስጠትና ለማራዘም ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ሳያመሩ በዚሁ በክልሉ ቅርንጫፍ ማግኘት እንደሚችሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉደዮችመምሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገ/ዮሐንስ በመግለፅ በእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑትን የክልሉ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር መልዕክታቸውን እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል።
"ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ ይህ ዕለት ትልቅ ታሪካዊ ቀን ነው። የኢትዮጵያን መብት የሆነውን ይህን ፓስፖርት ለማግኘት እጅግ በጣም ረጅምና አድካሚ ጉዞ ካደረጉ ወይንም ከብዙ ችግር በኋላ ነበር ሲያገኙ የነበረው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብም ልክ እንደ ማንኛውም የሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ወይም ህዝብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓስፖርት በመታወቂያው ማግኘት መብትና ግዴታው ነው ሆኖም ግን ለምሳሌ በኢ.ሶ.ክ ከፌርፌር ጅግጅጋ 1500 ኪ.ሜ ነው ከዚህ በተጨማሪም ከፌርፌር እስከ አዲስ አበባ አድካሚ ጉዞ በማድረግ ነበር ፓስፖርት ለማውጣት ይሄዱ የነበረው። በዛ ውስጥ ብዙ ችግሮች ነበሩ ለምሳሌ ሃጂና ኡምራ ለማግኘት አንድ አርብቶ አደር ያውም ጫካ የሚኖር የሐይማኖት ግዴታውን ለመወጣት ሲል የግድ ወደ ሃጅ መሄድ አለበት ፕሮሰሱን በሚጀምርበት ጊዜ ከቀበሌ መታወቂያ ሲያገኝ አንድ አካባቢ ብቻ አዲስ አበባ ሄዶ ነበረ ፓስፖርት ሲያገኝ የነበረው። እንግዲህ እንደሚታወቀው ይህ አርብቶ አደር ወረዳንና ከተማን አይቶ የማያውቅ ሲሆን ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ አዲስ አበባ ድረስ በመመላለስ ነበረ ፓስፖርት ለማግኘት የሚደርሱት ሌሎች በርካታ ችግሮችም እንደነበሩ ይታወቃል።"
ክቡር ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም "በተለይ ቢሮው ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፍተኛ መሻሻልና ጥሩ ሥራዎች ተሰርተውበት ነበር ምክንያቱም ቀደም ባለው ጊዜ ረጅም ጉዞ ተጉዞ ማግኘትም ጥሩ ነበረ ማለት ይቻላል ከዚህ በፊት ፓስፖርት ፈላጊዎች ተጉዘው ሄደው ላያገኙ የሚችሉባቸውም ጊዜያትም ነበሩ።ነገር ግን በቢሮው ከፍተኛ መሻሻል ስለተደረገ ይሄው ዛሬ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብ በጅግጅጋ ከተማ ፓስፖርት የማግኘት መብቱ ስለተረጋገጠ በመጀመሪያ ምሥጋናችንን ለአላህ እናቀርባለን በመቀጠልም ገደብ የሌለው ምሥጋናዬን ለፌዴራል መንግሥትና ለቢሮው አቀርባለሁ። የክልሉን መታወቂያ በዘመናዊ መንገድ የተሠራና በምንም አይነት መልኩ አመሳስሎ (ፎርጅድ) ሊሠራ የማይችል ሲሆን ይሄንን ከቢሮው ጋር ተስማምተን ያደረግነው ሲሆን በተጨማሪም ለሌሎች ክልሎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል አሠራር ነው ክልሉ የዘረጋው” በማለት አብራርተዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉደዮች መምሪያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገ/ዮሐንስ በበኩላቸው "የጅግጅጋ ኢሚግሬሽን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለኢትዮጵያዊያን ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪም በተለያዩ የውጪ ሃገራት ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያ ለሆኑት የኢትዮጵያ ሶማሌ ልጆች የትውልድ ካርድ የማደስ እና የመስጠት ለውጪ ዜጎች ደግሞ የኦንላይን ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘትና ለማራዘም አዲስ አበባ ሳይሄዱ እዚሁ ሊየዘገኙ የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
በተመሳሳይ የሃገራችንንና የክልሉን ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ገበያን ለማነቃቃት የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚመጡ ተጓዦች ሁሉም ቪዛዎች በኤሌክትሮኒክስ ወይም ኦንላይን ቪዛ መስጠት ተጀምሯል ዋና ዳይሬክተሩ ሲሉ ገልፀዋል።በመጨረሻም ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችም የናሙና ፓስፖርት ከፕሬዝዳንቱ እጅ በመቀበል በይፋ ሥራ መጀመሩን አብስሯል።