ባቢሊ(Cakaaranews)እሁድ፤ሰኔ 17/2010ዓ.ም በፋፈን ዞን እና አካባቢው በሚገኘው ባቢሌ ወረዳ የተሠሩት የሠፈራ ፕሮግረም በክልልና ዞን ሃላፊዎች ተጎብኝተዋል። ሃላፊዎቹ በ2010 ዓ.ም የመንደር ማሠባሰብ ትግበራ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በባቢሌ ቆለጂ ቀበሌ ውስጥ ተገኝተው አባወራዎችን እና የሥራ ውጤታቸውንም ተመልክተዋል። የሃላፊዎቹ ጉብኝት በዋናነት በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች የተከናወኑትን የጥምር ልማት ሥራዎች አፈፃፀም ክትትልለማድረግ እንደሆነም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተፋሰስ እና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን መሀመድ በጉብኝታቸው ወቅት ቅኝታቸውን እንዲህ ይገልፃሉ "በዋናነት ይህ ፕሮግራም በገጠራማ ቦታዎች ላይ በአርብቶ አደር ህይወት ላይ ጥገኛ የነበረውን ማህበረሠብ ወደ ከፊል አርሶ አደር የማምጣት አላማን ያነገበ ቢሆንም የኑሮ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑትን በመመልመል፣ በአንድ ቦታ በማሰባሰብ፣ ቤት በመሥራት፣ የእርሻ ቦታ በማዘጋጀት፣ የከብቶች ማደሪያ እና ማደለቢያ በመስጠት ውሃውን በማስገባት እዚህ ቦታ የሚሠፍሩ አባወራዎች የተሻለ ጥሩ ህይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። እሱም ተከናውኗል ከዚህም በኋል እነሱ የቀጣይ ወይም የወደፊት ኑሯቸውን የተሻለ ለማደረግ ጠንክረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥማቸው እንኳን እራሳቸውን እና ከብቶቻቸውን ለማትረፍ አቅም የተፈጠረላቸው ስለሆነ ነው " ሲሉ ተናግሯል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ጀማል ፋራህ ጉብኝቱን አስመልክተው ይህን ብለዋል "ዛሬ እየጎበኘን ያለነው በባቢሌ ወረዳ የተሠራውን የመንደር ማሠባሰብ ሥራዎች ነው። በዚህ ቦታ አስር አባወራዎች ሠፍረዋል አስር ሄክታር የከበቶች መኖ(Sudan Grass) ዘርተዋል በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ ሰብል በቆሎ ማሽላ ተዘርቷል ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ አትክልቶች እንደ ቲማቲም እና ጥቅል ጎመን የመሳሰሉትንም እየሠሩ ነው። ቦታው በመስኖ የሚለማ በመሆኑ ከምርታቸው ለገበያ የሚያቀርብም አቅም ይፈጥርላቸዋል እናም ይህ ፕሮግራም አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሠብ ክፍሎችን የሚደግፍ እና እራሳቸውን እንዲችሉ አቅምን የሚፈጥርላቸው ነው"።
በተያያዜም በባቢሌ ወረዳ የተከናወነው የሠፈራ ፕሮግራም በክልሉ አብዘኛው ቦታዎች የተተገበረው ሥራ አንድ አካል ሲሆን በባቢሌ ወረዳ የሠፈሩት አባወራዎች ከዚህ አሁን ባገኙት ሁለገብ ድጋፍ በቀጣይም ህይወታቸው የተሳካ እና ያማረ እንዲሆን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ሃላፊዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።