ጅግጅጋ(Cakaaranews)ቅዳሜ፤ግንቦት 25/2010ዓ.ም የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከስዊዘርላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር የሚተገብረው ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ የተባለ ፕሮጀክት በመጀመሪያ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሸበሌ ዞን አዳድሌ ወረዳ የተሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ይፋ አደርገዋል። ለፕሮጀክቱ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች በሸበሌ ዞን አዳድሌ ወረዳ ነዋሪዎችና እንስሳቶችን በተቀናጀ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚተገበሩ ስራዎዎች መሆናቸውን በጅግጀጋ ከተማ በተደረገደው የባለድርሻ አካላት ውይይት መድረክ ላይ ለማወቅ ተችሏል።
85 በመቶ አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሠብ በሚኖርበት የኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው ጅግጀጋ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመ ጀምሮ ከተለያዩ የሃገር ውስጥና ዓለምአቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ሲሆን ከስዊዘርላንድ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ጋር በተደረገ የሶስትዮሽ ስምምነት መሠረት ከሶስት ዓመታት በፊት ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ(one health iniative) የተባለ በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገም ተገልጿል። ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ እየተካሄደ ከሚገኘው የአቅም ግንባታ ስራዎች በተጨማሪም በክልሉ ሸበሌ ዞን አዳድሌ ወረዳ ሲከናወኑ የነበሩ አርብቶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን ፍላጎትና ችግሮችን መሠረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎች ተጠናቀው በትላንትናው ዕለት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የባለድርሻ አካላት የምክክር አውደ ጥናት ላይ ቀርቧል።
በጅግጀጋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የአዳድሌን ህብረተሠብ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች እውቅና መስጫ አውደ ጥናት ላይ የተገኙት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዲአዚዝ ኢብራሂም እንደተናገሩት በስዊዘርላንድ መንግሥት የሚደገፈው ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት ከአቅም ግንባታ ሥራዎች ጎን ለጎን በክልሉ ሸበሌ ዞን አዳድሌ ወረዳ ህብረተሠቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል እና በተቀናጀ መንገድ የሰው እና እንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚተገበር ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል።
በተያያዜም ዶ/ር አብዲአዚዝ ስለ ፕሮጀክቱ ገልፃ ሲሰጡም “በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ይህን ፕሮጀክት ውል የገቡትና ፈንድ የሚያደርገው የስዊዘርላንድ መንግሥት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የአቅም ግንባታውንም ሆነ ፕሮጀክቱንም ተደራሽ የሚያደርጉት በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በኩል ሲሆን የስዊዘርላንድ መንግሥትና የስዊዘርላንድ ባስ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። የሶስትዮሽ ስምምነት ነው ያደረግነው በዚህ የሶስትዮሽ ስምምነት ላይ ለሶሰት ተከታታይ ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች ስላሉ ከአቅም ግንባታው ጎን ለጎን ደግሞ ተማሪዎቻችን መጀመሪያም መምህራን ስለነበሩ አቅማቸውን የሚገነቡት ደግሞ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ ሲሆን 1ኛው የአዳድሌ ወረዳ ነው። ተማሪዎቻችን አዳድሌ ወረዳ ላይ ባደረጉት ጥናት የምርምር ሥራዎቻቸው ለምርቃት የሚበቁበትን ጥናታዊ ፅሁፎቻቸውንም ይሠሩበታል። ጥናቱ 3 መፍትሄዎችን ነው ያገኘው 1ኛው ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለአዳድሌ ወረዳ ህብረተሠብ በዝቅተኛ ወጪ ተደራሽ ማድረግ ነው። 2ኛው ህብረተሠቡ የሣንባ ነቀርሳ በሽታ በሚከሰትበት ወቅት ራሱን እንዴት እንደሚከላከል ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲሆን 3ተኛው ደግሞ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚዛመቱ በሽታዎችን በቡድን እየተናበቡ ሪፖርት አጠናቅሮ እንዴት እንደሚሠራ ሪፖርት ማድረግ ናቸው” ብሏል።
በመጨረሻም የጅግጅጋ ዩኒቬርሲቲ ዋን ሄልዝ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክቱ ለ12 ዓመታት እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን በአውደ ጥናቱም በአዳድሌ ወረዳ የተሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችም ቀርበው በአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።